Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቴፒ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ዳግም ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቴፒ መለስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ከረዥም ዓመታት በኋላ በዛሬው ዕለት ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀመሯል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታና በትራንስፖርት ዘርፍ የግል ባለሀብቶችን ማሳተፍ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አድርጓል።

ዛሬ ሥራ የጀመረው የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያ በሚኒስቴሩ ምላሽ ካገኙ 39 ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር የአካባቢውን ዕምቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ስራ መጀመር ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ከ1950 ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያ በ1990ዎቹ መጨረሻ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ ቆይቷል።

በአውሮፕላን ማረፊያው እስከ 55 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችሉ አውሮፕላኖች አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሏል።

በተስፋየ ምሬሳ

Exit mobile version