Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት የዘንድሮውን ክልላዊ የክረምት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

በዚህም የአፈር ለምነትን በመመለስ እንዲሁም የተራቆቱ አካባቢዎችና የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙ በማድረግ ሳቢና ምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ አረንጓዴ አሻራን ባህል እያደረገ መምጣቱን ጠቅሰው የተጀመረውን ተፈጥሮን የመንከባከብ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ1 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን፥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላላቸው የፍራፍሬ፣ የመኖ፣ የደንና የቡና ችግኞች ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

Exit mobile version