Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የበርካታ ሙያ ባለቤቷ ሔዋን (ዶ/ር)…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሔዋን ጌታቸው (ዶ/ር) ትባላለች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ምህንድስና አጠናቃቅለች።

የባቡር ምሕንድስና ትምህርት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሰጠት ሲጀምር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተመረጡ ሰባት ተማሪዎች መካከል አንዷ በመሆን የትምህርት እድል ማግኘት ችላለች።

በዚህም በኢትዮጵያ ብዙዎች ባልተሰማሩበት የባቡር ምሕንድስና የትምህርት መስክ 3ኛ ዲግሪዋን አጠናቅቃ አሁን ላይ በመደበኛ ሥራዋ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ውስጥ የምርምር ልማት ሥራ አስኪያጅ ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡

ባለትዳር እና የአንዲት ሴት ልጅ እናት የሆነችው ሔዋን (ዶ/ር) በአንድ ሥራ ብቻ ያልተወሰነች ለሌሎች አርአያ የምትሆን ጠንካራ ሴት ናት፡፡

ስዕል፣ ግጥም፣ የልብስ ዲዛይን እና ሌሎች የእጅ ጥበብ ሥራዎችን ከመደበኛ ሙያዋ ጎን ለጎን ታከናውናለች።

በልብስ ዲዛይን ሙያዋ ራሷን እና ቤተሰቧን በአልባሳት ታሳምራለች፤ በስዕል ጥበቧም ዐይነ ግቡ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን እየሠራች ቤቷን ታስውባለች፤ ለወዳጅ ዘመዶቿም ስጦታን ታበረክታለች።

ኔክስት ዲዛይን ባዘጋጀው የልብስ ዲዛይን ውድድር በፋንሲ ዘርፍ ያሸነፈች ሲሆን÷ በአጠቃላይ በውድድሩ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች፡፡

ሔዋን (ዶ/ር) ለጥበብ ሥራዎች ያላት መሰጠት ከልጅነቷ ጀምሮ ከአባቷ የተማረችው እንደሆነ በፋና ፖድካስት የእንግዳ ዝግጅት ላይ በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

ከሥራ ውጪ መሆን ያስጨንቀኛል የምትለው ሔዋን÷ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በስሌት ለማድረግ መጣሯ ዛሬ ለደረሰችበት የስኬት ጎዳና መሰረት እንደሆናትም ታስረዳለች፡፡

ሔዋን (ዶ/ር) በሕይወቷ መሆን የምትፈልጋቸውን ሁሉ ለማሳካት እንቅልፍ አልባና ፈታኝ ጊዜያትን ማሳለፏን ታስታውሳለች፡፡

“በተፈተንን ቁጥር ራሳችንን መፈተሽ እንጀምራለን” የምትለው ሔዋን (ዶ/ር)÷ በትጋት በመስራት የማይቻሉ የሚመስሉትን ማሳካት እንደሚቻል በሕይወቴ አረጋግጫለሁ ትላለች።

ሔዋን ጌታቸው (ዶ/ር) በፋና ፖድካስት የእንግዳ ዝግጅት ላይ የነበራት ክፍል ሁለት ቆይታ ነገ ምሽት በፋና ዲጂታል አማራጮች ይተላለፋል።

ክፍል አንድ 👉https://www.youtube.com/watch?v=y2bBLpa4jSA

በበጸሎት መንገሻ

Exit mobile version