Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለውን ጠቅላላ ሀብት 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር አሳደግኩ አለ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2017 ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን፥ በዓመቱ አመርቂ የሥራ አፈፃፀም በማስመዝገብ የገበያ ድርሻውን አሳድጓል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ515 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡን 1 ነጥብ 69 ትሪሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

በዚህም መሰረት ባንኩ የገበያ ድርሻውን 49 ነጥብ 6 በመቶ ማድረሱንም ነው የገለጹት፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ43 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትና ጠቅላላ ሀብቱ 2 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ባንኩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል።

በባንኩ ከተከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮች 92 በመቶ የሚሆነው በባንኩ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተከናወነ ሲሆን፥ ይህም በገንዘብ ደረጃ ከ13 ትሪሊዮን ብር በላይ መሆኑም ነው የተጠቆመው።

Exit mobile version