አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቅሬታዎች እንዲቀንሱ ተደርጓል አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው የአስተዳደሩን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባዋ እንዳሉት፤ በተቋማት 347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ብልሹ አሰራር፣ የተገልጋይ እንግልትና ምልልስ በማስቀረት የሚቀርቡ ቅሬታዎች እንዲቀንሱ ተደርጓል።
በተቋማት ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ከ2 ሺህ 147 በላይ የመንግስት ሰራተኞች በህጻናት ማቆያ ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨሪም በተቋማት ከ185 በላይ ካፍቴሪያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ እና ከ150 የሸማች ሱቆችን ወደ ሥራ በማስገባት ሰራተኞች የኑሮ ውድነቱን እንዲቋቋሙ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ከ21 ሺህ 46 በላይ የተገልጋይ ማረፊያ በማዘጋጀት ምቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባታቸውን ነው ያነሱት።
በሌብነትና ብልሹ አሰራር ተግባር ውስጥ የገቡ 4 ሺህ 965 አመራሮች፣ ፈጻሚዎች እና ተገልጋዮችን ተጠያቂ በማድረግ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከሰላምና ፀጥታ አንፃር የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጎልበት በአካባቢ ሠላም፣ በአብሮነትና ትብብር የሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ከ7 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማኅበረሰብ አቀፍ ምክክር መድረኮች ላይ ማሳተፍ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የሰላም ሠራዊት አደረጃጀቶችን እና የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
የወንጀል ድርጊቶችን በመቀነስ ረገድ ከሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት 11 ሺህ 517 የወንጀል ድርጊቶችና የፀጥታ ስጋቶችን የመለየት፣ የመከላከል እና እርምጃ የመወድ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።