አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት 55 ሺህ 729 ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው የአስተዳደሩን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የከተማዋን የቤት ፍላጎት ለሟሟላት የተለያየ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፤ በግለሰብና በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በመንግስት ቤቶችን የመገንባት ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
በዚህም በግለሰብ አልሚዎች 11 ሺህ 260 ቤቶች እና በሪል ስቴት አልሚዎች 30 ሺህ 507 ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ 8 ሺህ 786 ቤቶች መታደሳቸውን እና በመንግስት ለልማት ተነሺዎች 5 ሺህ 176 ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ በ2017 በጀት አመት 55 ሺህ 729 ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል ብለዋል።
በህገ ወጦች የተያዙ 453 የመንግስት ቤቶች እና 212 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በድምሩ 665 ቤቶችን በማስለቀቅ ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተላለፉም ጠቁመዋል።
በመንገድ ልማት ዘርፍ ረገድ በበጀት ዓመቱ የከተማውን የመንገድ መረብ ሽፋን የሚያሳድጉ፣ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጡ፣ የመንገድ ድህንነቱን የሚያረጋግጡ፣ ለኢንቨስመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ፣ የጉዞ ጊዜንና ገንዘብን የሚቀንሱ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
በዚህም 371 ኪሎ ሜትር የአስፓልት፣ 95 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮብል፣ 16 ነጥብ 1 ኪሎ ሜት የጠጠር፣ 107 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ተሰርቷል ብለዋል
እንዲሁም 3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ እና የድሬንጅ ግንባዎች እና 1 ሺህ 180 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልጸዋል።