አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ከ32 ሺህ በላይ የካካዎ ችግኝ አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ነው።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የካካዎ ምርት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዋወቅ ሥራዎች ተጀምረዋል።
የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የካካዎ ምርትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዋወቅ በሚሰራው ሥራ ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ በየደረጃው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በገበያ ተፈላጊ የሆኑ 558 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞችን ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 32 ሺህ የሚሆኑት የካካዎ ችግኞች ናቸው ብለዋል።
ችግኞቹን ለአርሶ አደሩ እና ለተቋማት እያከፋፈለ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ማዕከሉ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የቅመማ ቅመም እና የፍራፍሬ ዕጽዋቶችን ማባዛት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ካካዎ ቸኮሌትን ጨምሮ የተለያዩ ጣፋጭ ክሬሞችን ለማምረት በግብዓትነት ከሚያገለግሉ ተዋጽኦዎች መካከል ዋናው ነው።
በተስፋየ ምሬሳ