አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ቀደም ሲል ቫት የማይከፍሉ የነበሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ግብር ከፋዮች ወደ ቫት ስርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 233 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉ ተነስቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምክር ቤቱ እንዳሉት÷ የገቢ እድገቱ ምስጢር በጥንካሬና በእውቀት መስራት፣ የገቢ መሰረትን ማስፋት፣ ለታክስ ስወራ የሚያጋልጡ መመሪያዎችና አሰራሮች ማሻሻል እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነው፡፡
ለአብነትም ከዚህ ቀደም ቫት የማይከፍሉ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ግብር ከፋዮች ወደ ቫት ስርዓቱ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የግል ተቋማት ከሰራተኛ የደመወዝ ግብር እንደሚሰበስቡ ነገር ግን ለመንግስት ገቢ እንደማይደረግ ገልጸው÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የተሰወረ የግል ተቋማት የደመወዝ ግብር ተሰብስቧል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሰፊ የሥራ እድል እየተፈጠረ በመሆኑ አዳዲስ ግብር ከፋዮች ወደ ግብር ስርዓቱ እየገቡ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ውዝፍ የመሬት ሊዝ እና ውዝፍ ያልተሰበሰበ ግብር የት እንዳለ በመፈተሽ እንዲሰበሰብ መደረጉን ጠቅሰው፤ የኦዲት ግኝቶች እውነተኝነት እና ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል መዋቅራዊ አደረጃጀት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በዚህም ትክክል ያልሆኑ ወይም አላግባብ የተወሰኑ የኦዲት ግኝቶች ካሉ ለግብር ከፋዩ እንደሚወሰን እና አላግባብ የኦዲት ግኝት ተብሎ የተሰወሩ ግኝቶች ካሉ ደግሞ ለመንግስት ገቢ ይደረጋሉ ነው ያሉት፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣አዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ ፓርኮች እና ሌሎች በመዲናዋ የተሰሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ገቢ እያስገቡ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
መርካቶ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ አውጥተው ወደ ግብር ስርዓቱ እንዲገቡ መደረጉ የከተማው ገቢ እንዲጨምር ስለማድረጉም አንስተዋል።
ሆኖም ግን መርካቶን ጨምሮ አሁን ላይ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ግብር ስርዓቱ ያልገቡ በመኖራቸው በቀጣይ ወደ ግብር ስርዓቱ ለማስገባት እንደሚሰራ ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
በመሳፍንት እያዩ