Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት 350 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 2ኛ ቀኑን የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የከተማውን የ2018 በጀት አጽድቋል።

የበጀቱን መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ሬድዋን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የከተማው አጠቃላይ በጀት 350 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ108 ቢሊዮን ብር ወይም የ45 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

ከዘንድሮው አጠቃላይ በጀት 343 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን አንስተዋል።

በጀቱ በዋናነት ለደህነት ቅነሳ፣ ለዘላቂ ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እና ከከተማው ነዋሪ በተለያዩ መንገድ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ፣ ለአቅርቦት ድጎማዎችን እንዲሁም ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቁጠባን መሰረት ያደረገ ስራ ላይ የሚውል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ፣ ለቤት ልማት ስራዎች፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለስትራቴጂክ ዕቅዶች፣ ለመንገድ መሰረተ ልማት፣ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ታሳቢ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የመንግስት ወጪ በዋናነት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለሚያረጋግጡ ሥራዎች እንደሚውል አንስተዋል።

ከታክስ ገቢ 238 ነጥብ 93 ቢሊየን ብር ፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ 56 ቢሊየን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 46 ቢሊየን ብር፣ ከመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እና ከውጭ እርዳታና ብድር ደግሞ 6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ይገኛል ተብሎ ታቅዷል።

ከከተማው አጠቃላይ የ2018 በጀት ውስጥ 246 ነጥብ 3 ቢሊየን ወይም 70 በመቶው ለካፒታል ወጪ ይውላል ብለዋል።

በተመሳሳይ 91 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወይም 26 ነጥብ 2 በመቶው ለመደበኛ ወጪ የተያዘ ሲሆን 12 ቢሊየን ብሩ ወይም 3 ነጥብ 4 በመቶው ደግሞ መጠባበቂያ በጀት ተይዟል።

ለማዕከል ሴክተሮች 276 ቢሊየን ብር ወይም ከከተማው አጠቃላይ በጀት 78 በመቶውን እንደሚሸፍን የገለጹት የቢሮው ኃላፊ፥ ይህም ካለፈው ዓመት አንጻር የ91 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ለክፍለ ከተሞች ደግሞ 74 ቢሊየን ብር ወይም ከከተማው አጠቃላይ በጀት የ21 በመቶ በጀት ተደልድሏል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የተለያዩ ሽመቶችን ያጸደቀ ሲሆን፤ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ፣ መኮንን ያኢ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እና ኦሊያድ ስዩም የአዲስ አበባ የከተማ ቦታ ማስለቀቅ ጉዳዮችና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version