አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃ ሀብታችንን በቁጠባና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም አለብን አሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ሻንቶ ከተማ ከ208 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት አስጀምረዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ የፌደራል መንግስት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ በሀገር ደረጃ በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ችግር የነበረባቸውን አከባቢዎች ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ ሽፋን ችግር ያለባቸውን አከባቢዎች በዋን ዋሽ ፕሮግራም ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በአጠቃላይ 43 ፕሮጀክቶች በ2 ቢሊየን ብር በጀት እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
እንዲሁም በሆርን አፍሪካ ፕሮግራም ድርቅ በሚያጠቃቸው አከባቢዎች ስምንት ጥልቅ የከርሰ ምድር ውሃ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ በውሃ ልማት ፈንድ የሚሰሩ 12 ፕሮጀክቶች በ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ በገደብ፤ በዲላ እና ሻንቶ ከተሞች የሕዝብ ጥያቄ መነሻ አድርገው መሠራታቸውን አስረድተዋል።
በወላይታ ዞን ሻንቶ ከተማ አስተዳደር ከ208 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የጽዱ ኢትዮጵያ መርሐ ግብር አካል የሆነ የአከባቢ ፅዳትና ንጽሕና አጠባበቅ ስራ የሚያግዙ የፈሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ሲሆን የሕዝብ መጸዳጃ ቤት ግንባታ ጨምሮ በ8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እየተሰራ ይገኛል፡፡
በመጨረሻም ውሃ ሕይወት ነው የሚለውን ብሂል በተግባር ማሳየት የሚቻለው ሀብቱን በቁጠባና በፍትሐዊነት መጠቀም ሲቻል በመሆኑ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ይሄንን የውሃ ፕሮጀክት እንዲንከባከብ አደራ ሰጥተዋል።
በጌትነት ጃርሳ