Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ማንሰራራትና ከፍታ አንዱ ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት የኢትዮጵያ ማንሰራራትና ከፍታ አንዱ ማሳያ ነው አሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፡፡

የግብርና ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ሀሳብ በሸገር ከተማ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

በዚህም እስካሁን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ እድገት እያመጣ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለምግብነት፣ ለአካባቢ ውበት፣ ለደንና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ችግኞች እየተተከሉ ነው ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ባለፉት ዓመታት ምርታማነት ማደጉን፣ የአፈር መሸርሸር መቀነሱንና የደን ሽፋን ማደጉን ገልጸው፥ በዚህም ትላልቅ ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መካሄድ ከጀመረ ወዲህ የተተከሉ ችግኞች ምርት መስጠት መጀመራቸውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ሀብቷን ለልማት በማዋል የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠበቅ ላይ እንደምትገኝ አንስተው፥ የአረንጓዴ አሻራ ስኬትም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን እና የከፍታ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

Exit mobile version