Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ በ2018 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በ2018 በጀት ዓመት ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የዘርፉ የክልልና ከተማ አስተዳደር አመራሮች ዓመታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ እንደተናገሩት፥ ባለፉት ዓመታት በተቋም ግንባታ፣ በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአሠሪና ሠራተኛ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል።

የተቋም ግንባታው ሀገር የጀመረችውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚችል መልኩ መገንባቱን ጠቅሰው፥ የአሠራር ሥርዓቶችን የማሻሻል እና በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ በትኩረት መሠራቱን አብራርተዋል።

ይህም በ2018 በጀት ዓመት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አጽንኦት የሰጡት።

በክህሎት ልማት ረገድም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ የሰው ሀብት ልማት ሥራም ገበያ እና ፍላጎትን መሠረት በማድረግ መከናወኑን ተናግረዋል።

የሥራ እድል ፈጠራ ቁጥር ሪፖርት ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ህጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን ተግባራዊ ለማድረግ፣ ለኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ፋይናንስን ጨምሮ አስፈላጊ መንግስታዊ ድጋፎችን ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በ2018 በጀት ዓመት ሁሉም የዘርፉ ተቋማት የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢንተርፕራይዞች ምስረታ እና የሰልጣኞች ምዝገባ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የማካሄድ ሥራን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ፣በውጭ ሀገር እና በርቀት ሥራ ዕድል ፈጠራ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

Exit mobile version