አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ አቡ ዳቢ አዲስ በረራ ጀመረ።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እንዲሁም ዋና ስራ አስፈፃሚው መስፍን ጣሰውን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኤምባሲ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
አቶ መስፍን ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ወደ አቡ ዳቢ በረራ መጀመሩ አየር መንገዱ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር ያለውን ተነሳሸነት የሚያሳይ ነው፡፡
ከኢትሃድ አየር መንገድ ጋር በጋራ በመሆን ለመንገደኞች ምቹ ሁኔታን በማስፋት በሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች የተሻለ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም ገልፀዋል።
በየቀኑ የሚደረገው የአቡ ዳቢ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው ምስራቅና በገልፍ ቀጣና ያለውን ተደራሽነት ይበልጥ እንደሚያሰፋ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጽያ አየር መንገድ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅና በገልፍ ቀጣና በ13 መዳረሻዎች 100 ሳምንታዊ በረራዎችን እያደረገ ይገኛል።
በኤፍሬም ምትኩ