አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ህዝብን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
በክልሉ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የፓርቲና የመንግስት የ2017 በጀት አመት የስራ አፈፃፀምና የ2018 እቅድ የግምገማ መድረክ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል፡፡
የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና መዋቅሮች እውቅና የተሰጠ ሲሆን፥ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም መስክ በሚባል ደረጃ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል በግምገማው የጥንካሬና የድክመት መንስኤዎችን በጥልቀት መርምረን በመለየት አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም በአዲሱ በጀት ዓመት የጥንካሬ መሰረቶችን በማስፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ በየደረጃው ያለው አመራር በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት ለመስራት እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።
በክልሉ መንግስት የተሰጠው እውቅናና ሽልማት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስራን በጥራትና በብዛት መፈፀም የቻሉ አካላትን ለማበረታታት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡