አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚያከናውናቸው ሀገራዊ ተግባራት ላይ የቀድሞ ምሩቃን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ማህበር ሊመሰረት ነው፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ቀናት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እያከበረ መሆኑን ገልጸው፥ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ምሩቃን ማህበር ምስረታ በነገው እለት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ ምስረታ ዩንቨርሲቲው በሚያከናውናቸው ሀገራዊ ተግባራት ላይ የቀድሞ ምሩቃን ተቋማዊ በሆነ ሁኔታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ70 አመት ታሪኩ በልዩ ልዩ መስኮች ከ100ሺ በላይ ተማሪዎቸን አስመርቆ ለሀገር ማበርከቱን ጠቅሰው፥ በመጪው ቅዳሜ ከ2ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅም በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ከቀድሞ ምሩቃን መካከል ከፍ ያለ ሀገራዊ አበርክቶ ላላቸው ግለሰቦች እውቅና እንደሚሰጥም ነው የገለጹት፡፡
አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በመግለጫቸው ዩኒቨርሲቲው መነሻው የህዝብ ጤናን መጠበቅ እንደነበር አስታውሰው፥ ከመደበኛ መማር ማስተማር ባለፈ በልዩ ልዩ ዘርፎች በማህበረሰብ አገልግሎት የካበተ ልምድና ታሪክ አለው ብለዋል፡፡
በምናለ አየነው