አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) “ኪን ኢትዮጵያ – የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቀው የኪነ ጥበብ ቡድን የፊታችን እሁድ ወደ ቻይና ያቀናል፡፡
መርሐ ግብሩን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) እና አርቲስት ካሙዙ ካሳ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ÷ መንግስት የኪነ ጥበብ ዘርፉ በሀገር ግንባታ ሥራ ላይ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ትክክለኛ ገጽታዋን ለማስገንዘብ የምታደርገው ጥረት በኪነ ጥበብ መታገዝ እንዳለበት ገልጸው÷ የዚሁ አካል የሆነው የኪነ ጥበብ ቡድን የመጀመሪያ ጉዞውን ወደ ቻይና እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ቡድኑ በቻይና ቤጂንግ እና ናንጅንግ ከተሞች የኢትዮጵያን ባህል እንደሚያስተዋውቅ ጠቅሰው፤ መርሐ ግብሩ በመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ጭምር የተደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ለቱሪዝም መስፋፋትና ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ይህ የኪነ ጥበብ ጉዞ፤ በተለያዩ ዘርፎች ጥሩ ግንኙነት ያላቸውን የኢትዮጵያ እና ቻይና ትስስርን የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።
ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በበኩላቸው÷ ከ70 በላይ የሚሆኑ ከያኒያን የሚሳተፉበት የኪነ ጥበብ ጉዞ ከ39 ዓመታት በኋላ የሚደረግ ታሪካዊ ጉዞ ሲሆን ከ50 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃዎችና ጥበባት እንደሚቀርቡበት አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም በጉዞው ከትርኢቶች ባሻገር ኢትዮጵያ የአልባሳት ዲዛይን፣ የቡና ቅምሻ እና የአመጋገብ ባህሏን ታስተዋውቅበታለች ብለዋል።
አርቲስት ካሙዙ ካሳ በበኩሉ÷ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ አራት ወር የፈጀ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልፆ፤ በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ቱባ ባህሎች የሚያስተዋውቁ አዳዲስ ስራዎች ተካተውበታልም ብሏል፡፡
ከቻይና በተጨማሪ ወደ ሌሎች ሀገራትም በመጓዝ የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።
በመሳፍንት እያዩ