አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችሉ የግብርና መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል አሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን “አንድ እድል” ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ተቋማቸው የግብርናውን ዘርፍ ወደ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
እርሻን ከበሬ ለማላቀቅ በማህበር እና ዩኒየኖች ለተደራጁ ማህበራት ትራክተሮችን እና ኮባይነሮችን በመግዛት ለአርሶ አደሮች በኪራይ እንዲቀርብ፣ ስልጠና እንዲሰጥ እና የጥገና ሥራ እንዲሰራ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ አርሶ አደሩ ወደ ግብርና ሜካናይዜሽን እንዲሸጋገር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል።
አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የምርት እሴት ሰንሰለቶችን በማጠናከር ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
አርሶ አደሮች በግብርና ስራቸው ላይ ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ቢያጋጥማቸው በነጻ የስልክ መስመር በመደወል ማሳወቅ የሚችሉበት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ የሚያስችለው የዲጂታል ግብርና ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚኪያስ አየለ