አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ከተማ ነዋሪው ወጣት ዳዊት አየነው ከልጅነቱ ጀምሮ መታዘዝ መለያው፤ በጎ ማድረግ የነፍሱ ጥሪ ናቸው።
በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እና በአማኑኤል ሆስፒታል የነፍሱን ጥሪ እውን ያደረገባቸውን በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጥቷል።
ይህንን ተሞክሮውን ወደ ጎንደር ይዞ በመሄድ ለብዙዎች በመድረስ የልጅነት ጥሪውን እየኖረ ይገኛል።
በ2010 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ አስታማሚ የሌላቸውን ሰዎች በመርዳት የበጎ አድራጎት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
በሆስፒታሉ የተጀመረው በጎ ተግባሩን በማስፋት ቤታቸው ሆነው ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ማገዝ ጀምሮ ለበርካቶች ምርኩዝ ሆኗል።
ከዚያም ንፅህና መጠበቅ የማይችሉ አቅመ ደካሞችን በማገዝ በፈጣሪ ዘንድ የተወደደውን ‘ለሰዎች አለሁ’ ማለቱን ቀጠለበት።
ዳዊት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሀሳቡን የተቀበሉትን ሁለት እሱን መሰሎች ጨምሮ በሶስት ሰዎች በጎ ማድረጉን ተያያዘው።
ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ ሌሎች ብዙዎችን ከኋላው በማሰለፍ በአሁኑ ወቅት ‘ካለን ብናካፍል’ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማዕከል በመመስረት ለ20 ሺህ ወገኖች ድጋፍና እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል።
ማዕከሉ ከጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ራሳቸውን ችለው መመገብና መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ህሙማንና ልዩ ልዩ የጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች በመደገፍ ለችግራቸው እየደረሱ ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ዛሬ ባካሄደው የተማሪዎች ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ በ13 ዘርፎች ስኬታማ ስራ ለሰሩ እውቅና ሲሰጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት መንፈሱን ለሚያስደስተው ወጣት ዳዊት ልዩ የሰብዓዊ አገልግሎት ዘርፍ ዕውቅና ሰጥቶታል።
ወጣት ዳዊት የተሰጠው ዕውቅና የጀመረውን የበጎነት ስራ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጉልበት እንደሚሆነው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግሯል።
በምናለ አየነው