አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ከተማ ሕዝብ ለኮሪደር ልማት ስራ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል አሉ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኛው፡፡
አቶ ቻላቸው በከተማዋ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ÷ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሰላምና ልማትን የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በልማት ረገድ የፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ስራ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን እንዲሁም የከተማዋን ገፅታ መቀየር የሚችሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የመጀመሪያው ምዕራፍ መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ስራ እየተሰራ እንደሆነና የከተማዋ ሕዝብም ለኮሪደር ልማት ስራ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የኮሪደር ልማት በከተማዋ የስራ ባህልን መቀየሩን ያመላከቱት አቶ ቻላቸው÷ የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ለ46 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ከሰላምና ፀጥታ ስራዎች አንፃር በከተማዋ ለተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ሕብረተሰቡና የሃይማኖት አባቶች ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው÷ አሁንም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በከተማዋ የኮሪደር ልማት ምክንያት የተነሱ ዜጎችን በዘላቂ የመልሶ ማልማት ስራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በ311 ሚሊየን ብር የገበያ ማዕከል እየተገነባ መሆኑን ገልጸው÷ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምም 80 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በምናለ አየነው