አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ከ124 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በግብርና ለምቷል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
አቶ አወል በክልሉ ም/ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት ÷ በክልሉ በግብርና ዘርፍ በተከናወነ ሥራ ከ124 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል።
በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰበሰቡን ጠቁመው÷ በዚህም የእቅዱን 93 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በአረንጓዴ አሻራ 10 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የዕቅዱን 93 ነጥብ 9 በመቶ ማሳካት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በመኖ ልማት ከዚህ በፊት 2 ሺህ ሔክታር ብቻ ሲለማ እንደነበረ እና አሁን ላይ ወደ 25 ሺህ ሔክታር ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው ÷ በተከናወነው ሥራም 362 ሺህ ቶን በላይ መኖ መመረቱን አመልክተዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የክልሉ የወተት ምርት ከለውጥ በፊት ከነበረው 49 ነጥብ 9 ሚሊየን ሊትር ወደ 391 ሚሊየን ሊትር ማደጉን ነው ያስረዱት፡፡
በበጀት ዓመቱ 158 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን የተናገሩት አቶ አወል ÷ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 6 ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ130 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ እና 480 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡
በከሊፋ ከድር