አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዘመኑን የዋጁ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አዋሌ መሃመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በመዲናዋ የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የታገዙ፣ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም በመዲናዋ ዲጂታል ኢኮኖሚን ማሳላጥ የሚያስችሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ኃላፊው÷ በዚህም በኦንላይን የሚሰጡ ከ167 በላይ አገልግሎቶችን ጨምሮ 374 አገልግሎቶች ዲጂታል ተደርገዋል ብለዋል።
በዚህም ለሕብረተሰቡ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ቀሪ 312 አገልግሎቶችን ዲጂታል በማድረግ በመዲናዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የተጀመረውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አጠናክሮ በማስቀጠል ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የተቋማት አቅም ግንባታ እና የሰው ሃይል ስልጠና ላይ መሰራቱን ጠቁመው÷ በተለይም ኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
1 ሺህ 740 የሳይበር ደህንነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና በመስጠት ባለሙያዎች በዘርፉ ያላቸውን አቅም ማጎልበት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ሶፍት ዌር ማልማትን በተመለከተም 17 ያህል ተቋማት አሰራራቸውን ለማዘመንና ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ