አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሀገራት ከባሕላዊ አኗኗራቸው እና ማንነታቸው የተቀዱ በርካታ ባሕላዊ ምግቦች አሏቸው፡፡
የአፍሪካ ምግብ ሉዓላዊነት ህብረት ዳይሬክተር ሚሊዮን በላይ (ዶ/ር) እንደሚሉት ÷ አፍሪካውያን ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚለዩባቸው በርካታ አይነት ባሕላዊ ምግቦች አሏቸው፡፡
ይሁን እንጂ ባሕላዊ ምግቦችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ተፈላጊነታቸውን ከማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ውስንነት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡
ባለፉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ሼፎች ጉባዔና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ መድረክም መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው የአፍሪካ ሼፎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የአፍሪካ ሀገራት ባሕልና ምግቦች እንዲረዱ እንዲሁም በዘርፉ ያላቸውን ተሞክሮ እንዲለዋወጡ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በተለይም የአፍሪካ ባሕላዊ ምግቦችን አሰራር በሚገባ ለማስተዋወቅና ለመገንዘብ መድረኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ሼፎች ትብብራቸውን በማጠናከር ባሕላዊ ምግቦችን እና አሰራራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ እንደሚሰሩ በጉባዔው ተስማምተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ባሕላዊ የምግብ አሰራሮች በትምህርት ፖሊሲ እንዲካተቱና ወጣቱ ትውልድ በሚገባ ተረድቶ እንዲያጠናክራቸው በቁርጠኝነት ለመስራት ቃል ገብተዋል፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ የምግብ ሉዓላነት ህብረት ጋር በትብብር ያዘጋጁት የአፍሪካ ሼፎች ጉባዔ እና የሥርዓተ ምግብ የፖሊሲ ምክክር መድረክ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡
በጉባዔው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የምግብ ባለሙያዎች፣ የምግብ አምራቾች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የልማት አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።
በመላኩ ገድፍ