አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 7 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2013 በጀት ዓመት 20 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና 2013 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ ውይይት በክልሉ ምክር ቤት እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህ ውይይት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ።
በውይይቱ ላይ የገቢዎች የቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን÷በ2013 በጀት ዓመት 20 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ነው የገለፁት ።
በዚህም ከመደበኛ ገቢ 18 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር፣ከከተማ አገልገሎት ገቢ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በድምሩ 20 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አብራርተዋል።
የሚሰበሰበው ብርም የክልሉን ሰላም፣ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ሰፋፊ ስራዎችን ለማከናወን የሚውል መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በ2012 በጀት ዓመት ከመደበኛና ከከተማ አገልግሎት ለመሰብሰብ ከታቀደው 14 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ውስጥ 12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወይም የዕቅዱን 91 ነጥብ 34 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን የቢሮ ሀላፊዋ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

