Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ስፔን ከእንግሊዝ ተጠባቂው የፍጻሜ ጨዋታ …

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በስዊዘርላንድ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ ስፔን ከእንግሊዝ በሚያደርጉት ጨዋታ ነገ ምሽት ፍጻሜውን ያገኛል፡፡
የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ስፔን በዘንድሮ የአውሮፓ ዋንጫ መድረክ በግማሽ ፍጻሜው ጀርመንን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፋ ለፍጻሜ መብቃቷ ይታወሳል፡፡
ስፔን በግማሽ ፍጻሜው ጀርመንን አሸንፋ ለፍጻሜ እንድትበቃ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረችው ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ዋዜማ ላይ የማጅራት ገትር በሽታ ህመም አጋጥሟት የነበረችው አይታና ቦንማቲ ናት፡፡
የሁለት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊዋ ስፔናዊቷ የ27 ዓመት ተጫዋች አይታና ቦንማቲ በውድድሩ ጅማሮ ዋዜማ ሆስፒታል የገባች ቢሆንም ውድድሩ ሳይጠናቀቅ በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ወደ ሜዳ ተመልሳለች።
ከዚያም 120 ደቂቃ በተጓዘው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔንን ለፍጻሜ ያበቃች ብቸኛ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ሰርታለች፡፡
አይታና ቦንማቲ በነገ ምሽቱ የፍጻሜ ጨዋታ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ነች፡፡
ስፔን በውድድሩ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ጣሊያን፣ ቤልጂየም እና ፖርቹጋልን የመሳሰሉ ብሔራዊ ቡድኖችን ገጥማ ለፍጻሜው በቅታለች፡፡
ሌላኛዋ የፍጻሜ ተፋላሚዋ ሀገር እንግሊዝ በግማሽ ፍጻሜው ጣሊያንን በመርታት ለፍፃሜ መብቃቷ ይታወሳል፡፡
እንግሊዝን በበኩሏ ለፍጻሜው ለመድረስ ባደረገችው ጉዞ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዋን ሀገር ጣሊያንን ጨምሮ ስዊድን፣ ዌልስ፣ ኔዘርላንድስ እና ፈረንሳይን ገጥማለች፡፡
ሁለቱ የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዎች በፈረንጆቹ 2023 የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ተገናኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ስፔን እንግሊዝን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2023 የዓለም ዋንጫን ማሳካቷ አይዘነጋም፡፡
አሁን ደግሞ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በሌላ ውድድር በአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ተገናኝተዋል፡፡
ስፔን እንግሊዝን በሌላ የፍጻሜ ጨዋታ በማሸነፍ በድጋሚ የበላይነቷን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ እንደምትገባ ሲጠበቅ እንግሊዝ በበኩሏ በ2023 የዓለም ዋንጫ በስፔን የደረሰባት ሽንፈት በአውሮፓ ዋንጫ እንዳይደገምባት እና ሌላ ዋንጫ በድጋሚ በስፔን ላለመነጠቅ ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡
ለ14ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የሴቶች የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ነገ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ስፔን ከእንግሊዝ በሚያደርጉት ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ
Exit mobile version