Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሞጆ ደረቅ ወደብን በማልማት የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሞጆ ደረቅ ወደብን በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ሥራዎች በልማት የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን።

የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሰራተኞች፣ በፕሮጀክቱ የሚሰሩ የውጭ ዜጎችና የገዳ ኢኮኖሚ ዞን ሰራተኞች በሞጆ ደረቅ ወደብና ገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የአረንጓዴ አሻራ የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም ያስችላል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሞጆ ደረቅ ወደብን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ለማስተሳሰር የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ማዕከል በማድረግ የሎጂስቲክስ ሥራዎችን ለማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በወደቡ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሥራን በማጠናከር የሎጂስቲክስ ሥራዎችን በአስተማማኝ መልኩ ማከናወን ያስችላል ነው ያሉት።

ከውጪ ከሚገባው እቃ 90 በመቶው የሚስተናገደው በሞጆ ደረቅ ወደብ መሆኑን ጠቁመው፥ የወደቡን አቅም ለማሳደግ የተጀመረውን የማስፋፊያ ሥራ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ የአካባቢና ማሕበረሰብ ጥበቃ አማካሪ አቶ ብርሃን ኪዳን በበኩላቸው፥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የአፈር ለምነትንና የአካባቢ ሚዛንን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አንደሚጫወት ጠቅሰዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ከ10 ሺህ በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፥ ደረቅ መደቡን የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version