አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 373 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል።
የክልሉ የትምህርቱ ዘርፍ ባለድርሻዎች፣ መምህራን እና አመራሮች በተገኙበት ክልል አቀፍ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ትምህርት ቢሮ ሀላፊ በየነ በራሳ በመድረኩ እንዳሉት፤ የትምህርት ተደራሽነት ለማስፋት የትምህርት ቤቶች ግንባታ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።
ሀገርን መገንባት የሚቻለው ትውልድን በትምህርት መቅረፅ ሲቻል እንደሆነ ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ 373 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል ብለዋል።
በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የበቁ መምህራንን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ አንስተው፤ መምህራኑን በተቋማቱ በአግባቡ ከማሰማራት አንፃር ውስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ከ900 በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ መምህራንን ማሰልጠን ተችሏል ያሉት አቶ በየነ በራሳ፤ ባለፉት 3 ዓመታት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በተሰራ ስራ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል።
የመጣው ለውጥ ዘርፉ ከሚፈልገው አንጻር በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የተጀመሩ የትምህርት ማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በነገዎ ብዙነህ