Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል- አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ ከክልሉ ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ እስካሁን መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት ተመልሰዋል፡፡

የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከገቡ ታጣቂዎች መካከል 5 ሺህ 200 ለሚሆኑት የተሃድሶ ስልጠና በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በልማት ተሰማርተው ህብረተሰቡን እንዲክሱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም የተገኘውን ሰላም በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የሰላም ጥሪውን ባልተቀበሉ አካላት ላይ የተጀመረውን የህግ የማስከበር ተግባር በማጠናከር ሰላምን ለማጽናት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በከተሞች ከመሬት፣ ከኢንቨስትመንት እና ንግድ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ አንስተዋል።

የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማፋጠንም የግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ትስስር በማጠናከር የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የምክር ቤት አባላት በየደረጃው ያለውን አስፈፃሚ አካላት በመከታተል፣ በመቆጣጠርና ሰላምን አፅንቶ በማዝለቅ የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንዲወጡ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።

Exit mobile version