Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዓላማችን ጥገኝነትንና ተረጂነትን ማስቀጠል ሳይሆን አፍሪካ ራሷን እንድትችል ማድረግ ነው – ጂኦርጂያ ሜሎኒ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓላማችን ጥገኝነትን እና ተረጂነትን ማሥቀጠል ሳይሆን አፍሪካ ራሷን እንድትችል ማድረግ ነው አሉ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጉባዔውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በዘርፉ ባስመዘገበችው የሚደነቅ ተግባርና ለአፍሪካዊያን ካላት የመሪነት ሚና አንጻር የምግብ ሥርዓት ውጥኖችን ዳር እንደምታደርስ በመታመኑ ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ ላይ የኢትዮጵያን ስኬት በማድነቅም አምራችነትንና ፍትሀዊ የምርት ግብይትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት አሁን ላይ በዓለም ከ10 በመቶ እንደማይበልጥና ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ያለው አፍሪካ ውስጥ መሆኑን ገልጸው፥ ችግሩን ለመፍታት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚጠይቅ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ የምግብ ራስን የመቻል ሂደት እንዲሳካ ሀገራቸው እና የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፥ ዓላማችን አፍሪካ ተረጂ ሆና እንድትቀጥል ሳይሆን ራሷን በምግብ የቻለች አህጉር እንድትሆን ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ በንግግራቸው የምግብ ሥርዓት አለመመጣጠን ብቻውን የድህነት መገለጫ አለመሆኑን ገልጸው፥ የምግብ ሉዓላዊነት የኃይል ሚዛንን ለማስተካከል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።

በመሳፍንት ብርሌ

Exit mobile version