አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ኢትዮጵያ በምግብ ስርዓት ያከናወነቻቸውን ተግባራት እና ያገኘችውን አበረታች ውጤት ለዓለም አሳይታበታለች አሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ ጉባኤውን አስመልክቶ ከተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመግለጫቸው እንዳሉት፤ ከመላው ዓለም መሪዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በጉባኤው ላይ መገኘታቸው ከየአቅጣጫው የምግብ ሥርዓትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ጉባኤው የምግብ ስርዓትን ስኬታማ ለማድረግ ተገቢው የፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር ለመምከር ትልቅ ሚና አለው በማለት ገልጸው፤ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ በቀላሉ የሚተው ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት ግቡን ለማሳካት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተንጸባርቋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያስመዘገበች ውጤት የተቀመጠው ግብ መዳረሻ ባለመሆኑ ግልፅ አሰራር ተዘርግቶ ወደ ተግባር የገባው የምግብ ስርዓት ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
እስካሁን ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለይተን በቀጣይ ጥረታችን ውጤታችንን ከፍ ለማድረግ እንተጋለን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የዘረጋችው አሰራር ስርዓት ከአጋር አካላት ግቦች ጋር በአመዛኙ የሚጣጣም በመሆኑ በቅንጅት ለመሥራት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
አሚና መሀመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ጉባኤ ከአራት ዓመት በፊት የገባቻቸውን ቃል ኪዳኖች የምትተገብርበት መንገድ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በተለይም የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ በርካታ አካታች ሰው ተኮር ተግባራት ስራዎቿ የሚደነቁ ናቸው ሲሉ ተናግረው፤ ይህም ለምግብ ስርዓት ትግበራ የመንግስት ቁርጠኝነት ማሣያ መሆኑን አንስተዋል።
በዓለም ላይ ያለው የምግብ ስርዓት ብዙ ተግዳሮቶች እንደተደቀኑበት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የቀየሰችው መንገድ ከችግሩ ለመውጣት ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ምርታማነትን ማሳደግ፣ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን አቅም ማጎልበት፣ የገበያ ትስስሩን ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ማረጋገጥ ውጤታማ የምግብ ስርዓት ለመገንባት ወሣኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የአነስተኛ አርሶ አደሮች አቅም መጎልበት የማህበረሰቡን የምግብ ስርዓት ህልውና ይታደጋልም ነው ያሉት።
እየተከሰቱ ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ከረሃብ ነፃ ዓለምን እውን ለማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት አዳጋች ቢሆንም ኢትዮጵያ በሄደችበት ፍጥነት ብዙ ሀገራት የምግብ ስርዓትን ካሻሻሉ የተያዘው ግብ በሂደት ይሳካል ብለዋል።
በመሳፍንት ብርሌ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!