Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጉባኤው ኢትዮጵያ ልምድ ያካፈለችበትና የመፍትሔ አካል ሆና የቀረበችበት ነበር – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያስተናገደችው 2ኛው የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ ልምዷን ያካፈለችበትና ለምግብ ሥርዐት መስተካከል መፍትሔዎችን ያቀረበችበት ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመቀናጀት ያዘጋጁት የዓለም የምግብ ሥርዐት ጉባኤ በርካታ የሀገራት መሪዎች፣ የግብርናው ዘርፍ ተመራማሪዎችና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በታደሙበት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡

በጉባኤው ባለፉት ዓመታት በምግብ ስርዓት ለውጥ ረገድ የታዩ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተገምግመው ቀጣይ አቅጣጫዎች ተመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጉባኤዉን ከማስተናገድ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሄደችበትን ርቀት በመልካም ተሞክሮነት አካፍላለች፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በየዓመቱ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የምትተክለውን በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችና ከምግብ ስርዓት መረጋገጥ ባሻገር ያስገኛቸው ውጤቶች በልምድነት ቀርበዋል፡፡

ጉባኤዉ የ2030 (እ.አ.አ) የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት በምግብ ስርዓት ረገድ ስኬት ሊመዘገብ በሚችልበት አግባብ ላይ በስፋት የመከረ፣ በርካታ አማራጭ ተሞክሮዎችን የዳሰሰና ቀጣይ ትኩረቶችን ያመላከተ ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡

በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ዐሻራ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ከጉባኤዉ ጎን ለጎን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን ለማጠናከር መድረኩን በእጅጉ ተጠቅማበታለች፡፡

በተጀመረዉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በግብርናዉ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን አሳይታበታለች፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ከ150 በላይ አህጉራዊና ዓለማቀፍ ጉባኤዎችን ያስተናገደችዉ ኢትዮጵያ በጀመረችዉ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የዓለም የኮንፈረንስ ቱሪዝም የትኩረት ማዕከል ሆና ቀጥላለች፡፡

የከተሞችን ገጽታ በእጅጉ መለወጧና የአገልግሎት ዘርፉ እየጎለበተ መምጣት፣ የሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ባህል የዳበረ መሆን፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት መዲና ባለቤት መሆን፣ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዐቅም እየጎለበተ መምጣት መሰል ትልልቅ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ዕድሎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ለጉባኤዉ በስኬት መጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፀጥታ ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም እንግዶች ለጉብኝትና ለልምድ ለውውጥ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በክብር ላስተናገዱ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መንግሥት የላቀ ምስጋና ያቀርባል፡፡

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Exit mobile version