Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ያስተካክላል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እየተስተዋለ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፡፡

በአማራ ክልል የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እየተካሄደ ሲሆን ርዕሰ መስተዳደሩ በኮምቦልቻ ከተማ ችግኝ በመትከል ዐሻራቸውን አኑረዋል።

በዚህ ወቅት አቶ አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢኮኖሚ አቅምን ሊያጠናክሩ የሚችሉ እጽዋት ችግኞች እየተተከሉ ይገኛል ብለዋል።

ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች ምርት በመስጠት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለክልሉ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል እንደ ሀገር የተጀመረውን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ለማጠናከር በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን እንደሚከላከል ገልጸው፤ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ መሬት መንሸራተት እና ለሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎችን መከላከል ዛፍ በመትከል እንደሆነ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር ተሻጋሪ ችግሮችን እንደሚያስከትል በመጠቆም፤ ሀገራት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመውሰድ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

Exit mobile version