አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ጣና ነሽ ፪ ከመነሻዋ እስከ መድረሻዋ የታየው ድንቅ አቀባበል የታሪካችን አካል ሆኖ ተመዝግቧል አሉ።
ከጅቡቲ ዶራሌ ወደብ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም የተነሳችው ጣና ነሽ ፪ ጀልባ በዛሬው ዕለት የየብስ ጉዞዋ መጨረሻ ወደ ሆነው ባህር ዳር ከተማ ስትደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል።
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት፤ ጣና ነሽ ፪ የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የአብሮነት ማሳያ ምስጢር ሆናለች።
ከጅቡቲ ወደብ ተነስታ ባሕር ዳር እስክትደርስ የታዩ ክስተቶች የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለወራት በተደረገው የጀልባዋ ጉዞ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ጣና ነሽ ፪ በደረሰችበት ሁሉ በፍቅር እየተቀበሉ በፍቅር የሸኟት ኢትዮጵያውያን ሃብት ናት ብለዋል።
ጣና ነሽ ፪ ከመነሻዋ እስከ መድረሻዋ የታየው ድንቅ አቀባበል የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን ደማቅ ምልክት እና የታሪካችን አካል ሆኖ ተመዝግቧል ነው ያሉት።