አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀይማኖት ተቋማት አብሮነትን በማጠናከር የሀገርን ሰላም ለማጽናት ያላቸውን ሚና ማጠናከር ይገባል አለ የሰላም ሚኒስቴር፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ “ሃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሐረር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄደ ይገኛል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የሀይማኖት ተቋማት ባለፉት ዓመታት የሀገርን ሰላም ለማጽናት በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ስለ ማህበረሰብ መፈቃቀርና ስለ ሰላም ከህዝብና ከመንግስት ጋር በጋራ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለእድገትና አብሮነት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ይህንን ተግባር በይበልጥ በማስቀጠል ለሀገር አንድነት በጋራ ጥሩ ውጤት ማምጣት አለብን ብለዋል።
ጉባኤው ሰላም በሀገሪቱ በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጥልና ህዝቡ የሰላም ባለቤት ሆኖ እንዲሰራ የሃይማኖት አባቶችና ምዕምናን ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
በጉባኤው ላይ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።
በጌታሰው የሽዋስ