አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ7 ሺህ 471 መምህራን የክረምት ልዩ የመምህራንና የትምህርት አመራር አቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትልና የመምህራን እና ትምህርት ዘርፍ ኃላፊ ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ የመምህራንና የትምህርት አመራር አቅም ግንባታ ስልጠና ለተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን ተሰጥቷል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በቀጠለው ስልጠናም በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት መስኮች ላይ እያስተማሩ ያሉ ሁሉም መምህራን ስልጠናውን እየተካፈሉ መሆናቸውን አንስተው÷ የፊዝክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ሂሳብና እንግሊዘኛ መምህራንም ስልጠናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የስራና ተግባር ትምህርት የመምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና አካል መሆናቸውን ጠቁመው÷ መምህራንና የትምህርት አመራሮ በተመረጡ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ስልጠናው መምህራን በትምህርት ተቋማት ከወሰዷቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ አዳዲስ እሳቤዎችን በማከል ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥሩ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
በሚኪያስ አየለ