Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ እና ቱርክሜኒስታን በፋይናንስና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቱርክሜኒስታን በፋይናንስና ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከቱርክሜኒስታኑ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ማሜትጉሊ አስታናጉሎቭ ጋር በቱርክሜኒስታን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው ሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ጉባኤ ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የሀገሪቱን እምቅ አቅም ለማውጣት በዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አትራፊ የሆነ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው÷ ማሻሻያው ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እና ኢኮኖሚውን ወደ ውጭ ንግድና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ሁለገብ ስትራቴጂ መሆኑን አመልክተዋል።

ሎጂስቲክስና ፋይናንስን ጨምሮ ቁልፍ ዘርፎችን ነጻ በማድረግ ለንግድ ክፍት የሆነ እንዲሁም ኢንቨስትመንቶችን ለማሳደግ የሚያስችል ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፍ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

የቱርክሜኒስታን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ማሜትጉሊ አስታናጉሎቭ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ማሻሻያዎች ያላቸውን ጥልቀትና ዓላማ በማድነቅ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት ተምሣሌት ነው ብለዋል።

እንዲህ አይነት አስተማማኝ፣ ግልጽና በማሻሻያ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ አስተዳደር መዘርጋት ጂኦግራፊያዊ ጉዳቶችን ለማሸነፍ እጅግ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑንም አንስተዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የባህር በር እጦት የካፒታል ወጪን እንደሚያንር፣ የኢንቨስትመንት ስጋትን እንደሚጨምር እና ለትላልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ወሳኝ የሆነውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የሚያደናቅፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ጠንካራ የፋይናንስ አጋርነት ተጨባጭ የሎጂስቲክስና የንግድ ፕሮጀክቶችን መደገፍ እና አዲስና ጠንካራ የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች መክረው በፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version