አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ የተመሠረተ ነው አሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ፡፡
ሚኒስትሩ ከቱርክሜኒስታን ፓርላማ ሊቀመንበር (ሜጅሊስ) ዱንያጎዘል ጉልማኖቫ ጋር በባህር በር ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የፓርላማ ግንኙነቶችንና ቀጣናዊ ትስስርን በመጠቀም የባህር በር አለመኖር የሚያስከትላቸውን ከባድ የልማት ተግዳሮቶች ለማሸነፍ በሚቻልባቸው ተጨባጭ ስልቶች ላይ መክረዋል፡፡
አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጥያቄው በሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መሰረት ባላቸው መንገዶች የሚመራ የቀጣናዊ ብልፅግና መፍትሄ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጥረት በራሷ ተነሳሽነት የምታበረክተው አስተዋጽኦ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በፓኪስታን ተቀማጭነታቸውን በማድረግ በቱርከሜኒስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር ) ÷ ኢትዮጵያ የባህር በር መብት ጥያቄዋን በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ ትቀጥላለች ብለዋል።
ዱንያጎዘል ጉልማኖቫ በበኩላቸው ÷ አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የህግና የንግድ ማዕቀፍ የባህር በር የሌላቸው ሀገራትን ከፍተኛ ተጋላጭነት በአግባቡ ከግምት ያስገባ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በዓለም ንግድ ድርጅትና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአንድነት በመንቀሳቀስ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲኖር መታገል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በስትራቴጂካዊ ትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በፓርላማዎች መካከል ለመመስረት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡