አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት ለዓለም ፈተና እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረዋል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ባወጣው መረጃ እንዳስታወቀው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ የአህጉሪቱ ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም የሚያስችል ተግባራት እያከናወኑ ነው።
በአብነትም የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ከከባቢ አየር ጋር በተናበበ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጿል።
ከኮሪደር ልማቱ በተጨማሪ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ፕሮግራም ከተማዋን ንጹህና ለኑሮ ምቹ የሚያደርግ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ አንስቷል።
በተመሳሳይ በሴኔጋል ዳካር ከተማ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ አውቶቡስ፣ በሩዋንዳ ኪጋሊ የሚተገበበረው አረንጓዴ የሕንፃ ሕጎች የአየር ንብረት ለውጥን ጫና ለመቋቋም የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና እየተወጡ እንደሆነ አስገንዝቧል።
በአፍሪካ የአየር ንብረት ጫናን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት እና ስጋቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ተሞክሮ ሆነው ቀርበው ትምህርት ይወሰድባቸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በታዳሽ ሀይል አጠቃቀም እና በሌሎችም ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶችን በጉባኤው ለማቅረብ ተዘጋጅታለች።
ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በዘርፉ የሰሯቸውንና ያስመዘገቧቸውን የመፍትሔ ሀሳቦች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባዔው ሲጠናቀቅ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ተስማምተው የጋራ አቋም በማውጣት በመጪው ህዳር ወር በሚካሄደው የኮፕ 30 የአየር ንብረት ጉባኤ የአህጉሪቱን አቋም ይዘው ይቀርባሉ።
በሶስና አለማየሁ