Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለኢጋድ የውሃማ አካላት ምጣኔ ሀብት አጀንዳ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የብሉ ኢኮኖሚ አጀንዳ እና ዘላቂ የዓሣ ሀብት ስትራቴጂ ትግበራ ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች አለ የግብርና ሚኒስቴር።

የኢጋድ ቀጣናዊ የዓሣ ሀብትና የውሃማ አካላት ምጣኔ ሀብት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ እንደታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የውሃ ሃብት ፕሮጀክቶች አዳዲስ የውኃ እድሎችን እየፈጠሩ ነው።

የኢትዮጵያን የ10 ዓመት የአሳ ሀብትና የከርሰ ምድር ልማት ዕቅድ ጠቅሰው፥ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ውኃማ አካላትን አቅም በማጎልበት የዓሣ ሀብት ልማት ላይ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዓሣ፣ የማር፣ የእንቁላል እና የወተት ሀብት ልማት ላይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የኢጋድ የአሳ ሀብት ፎረም ኤጀንሲ እና ቀጣናዊ የክትትልና ቁጥጥር ማስተባበሪያ ማዕከልን ለማቋቋም ምክክር እየተደረገ ይገኛል።

የኢጋድ የአካባቢ ጥበቃና ግብርና ዘርፍ ዳይሬክተር ዳህር ኤሊ በበኩላቸው፥ በቀጣናው ዓመታዊ የዓሣ ምርት እምቅ አቅም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን በላይ ቢሆንም፥ አሁን ላይ እየተመረተ ያለው 1 ሚሊየን ቶን ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ደካማ መሠረተ ልማት እና የዓሳ ምርት አጠቃቀም ውስንነት ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

Exit mobile version