Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

155 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 155 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እንዳሉት÷ በገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች እንዲሁም በከተሞች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በተከናወነ ሥራ 501 ሺህ 588 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከዋናው ሃይል ቋት 148 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን እንዲሁም ከዋናው ሃይል ቋት የራቁ 7 ቀበሌዎችን በኦፍ ግሪድ ከፀሃይ ኃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ የተቋሙ ደንበኞች ቁጥር ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ መድረሱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የድህረ ክፍያ፣ ከ900 ሺህ በላይ የቅድመ ክፍያ እና 43 ሺህ በላይ የስማርት ሜትር ተጠቃሚ ደንበኞች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 15 ሺህ 865 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጅምላ ተገዝቶ ለተጠቃሚዎች መሰራጨቱን ጠቅሰዋል፡፡

ከ4 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 7 ሺህ 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የማሰራጫ መስመሮች መልሶ ግንባታና የ1 ሺህ 984 ትራንስፎርመሮችን አቅም ማሻሻል መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version