Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ ተመደቡበት የተልዕኮ መስክ ይገባሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ተመደቡበት የተልዕኮ መስክ ይገባሉ አለ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጦሽኔ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተመደቡባቸው የአጠቃላይ የተግባር እና የምርምር መስኮች ገብተዋል፡፡

በተለያየ ደረጃ ቢሆንም ሁሉም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ተልዕኮ መስካቸው መግባታቸውን ገልጸው÷ ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ተልዕኮ መስካቸው እንዲገቡ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮ መስክ መለየት ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ለማፍራት ይሰራል ነው ያሉት።

ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመምጣት ለተማሪዎች ስልጠና እንዲሰጡ እና ስታርትአፖች እንዲፈጠሩ የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች ወደ ተልዕኳቸው መግባት ተማሪዎች የአካባቢያቸውን ጸጋ በመለየት ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀርቡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምርምር ዘርፍ የተለየው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር)÷ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በመምህራን ትምህርት፣ በጤናና እና በግብርና ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የትምህርት ፕሮግራሞችን እና የሰው ሀይል ክለሳ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የሚታጠፉ ወይም አዲስ የሚጀመሩ የትምህርት ፕሮግራሞች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

በ2021 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ህጎች እና የሰነድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአፕላይድ ሳይንስ ዘርፍ የተለየው የአርሲ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሰጦፋ ባቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እንዲሁም ጤና ላይ ይሰራል ነው ያሉት።

የትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ከንድፈ ሀሳብ በዘለለ ተግባር ተኮር ትምህርቶች ላይ ሰፊ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

ተማሪዎች በኢንተርንሽፕ እና በኤክስተርንሽፕ በኢንዱስትሪዎች እንዲለማመዱ ከ44 ኢንዱስትሪዎች ጋር ስምምነት ተደርጓል ብለዋል።

በመሳፍንት እያዩ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version