Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የስራ አጋሮች እንዲሁም አድናቂዎች ተገኝተዋል።

አርቲስት ደበበ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን÷ በቴአትር፣ በፊልም እና በጋዜጠኝነት ሙያ በርካታ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች አቅርቧል፡፡

ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ አዘጋጅ እና ተዋናይ ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው አርቲስቱ÷ በቴአትር መድረኮች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

አርቲስት ደበበ መጀመሪያ በቴአትር መድረክ የታየው በመንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻ ሲሆን÷ በመቀጠልም በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል፡፡

ከመጽሐፍት ስራዎቹ መካከል የተዋናይ ዝግጅትና የደም እንባ በትርጉም ያዘጋጃቸው ሲጠቀሱ፤ በመድረክ ቴአትር ከ40 በላይ ተውኔቶች ላይ ተሳትፏል፡፡

ከእነዚህ ስራዎቹ መካከል ጠልፎ በኪሴ፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ ጠያቂ፣ የቬኑሱ ነጋዴ፣ ናትናዔል ጠቢቡ፣ እናት አለም ጠኑ፣ የበጋ ሌሊት ህልም፣ ንጉስ ሊር፣ አመት ከአንድ ቀን፣ እኔ እና ሃያ ሰባት ገረዶቼ እንዲሁም የአዛውንቶች ክበብ ይገኙበታል።

በፊልሞች ስራዎች ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር፣ ሻፍት ኢን አፍሪካ፣ ጉማ፣ ዜልዳ፣ ዘ ግራንድ ሪቤሊየን፣ ዘ ግሬቭ ዲገር፣ ሬድ ሊቭስ እና ስጋ ያጣ መንፈስ ከአርቲስት ደበበ እሸቱ ህያው ስራዎች መካከል ናቸው።

በተለያዩ ስራዎቹ አድናቆት የተቸረው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ÷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል፡፡

አርቲስቱ ሀገር ችግር ውስጥ በሆነችበት ጊዜ ሁሉ ከፊት በመቆም በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን÷ በበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ግንባር ቀደም ነበር፡፡

Exit mobile version