Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን ፕሬዚዳንት ጋር መከሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን ፕሬዚዳንት አሲፍ አሊ ዘርዳሪ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ በቅርቡ በፓኪስታን ለደረሰው የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ስም የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ አካባቢ ጥበቃ እና በሕግ ዘርፎች የተደረጉት መሰረታዊ ማሻሻያዎችን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በግብርና እና በባንክ ዘርፎች ያለውን ሰፊ አቅም በማውጣት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹና ማራኪ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
የሀገሪቱ እድገት ማሳያ የሆነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬትም በውይይቱ ተነስቷል።
አምባሳደሩ መርሐ ግብሩ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ ደንን በማልማትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት አሲፍ አሊ ዘርዳሪ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የቀጥታ በረራ መጀመሩ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በቱሪዝምና በንግድ ላይ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ቁልፍ ክንውን ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን አስደናቂ እድገት ለመመልከትና እያደገ የመጣውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር በቅርቡ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸውንም ኤምባሲው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Exit mobile version