አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሆቴሎች በአዲስ አበባ በመጪው ጳጉሜን እና መስከርም ወር ለሚካሄዱ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ ነው አለ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት፣ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ እና 2ኛው የካሪቢያንና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የፊታችን ጳጉሜንና መስከርም ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የመዲናዋ ሆቴሎች የጉባዔ ተሳታፊ እንግዶችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰሩ ነው፡፡
ሆቴሎች የኢትዮጵያን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል የተላበሰና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁና የኢትዮጵያን ባህል የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ ውይይትና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም የጉባዔው ተሳታፊዎች በቆይታቸው አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉ የቡና አፈላል ሥርዓት፣ ባሕላዊ ምግቦች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎችና ሌሎች ኩነቶችን ለእንግዶች ለማስተዋወቅ ዝግጅት ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ሆቴሎች ለጉባዔ ተሳታፊ እንግዶች ለሚሰጡት ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ለማድረግ መስማማታቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥ እንዳያጋጥም የመዲናዋ አመራሮች ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግ መሰል ጉባዔዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ