Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከወጪ ንግድ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዷል

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም በማሳደግ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል አሉ።

በ2017 በጀት ዓመት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ዘርፍ ትላልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን የገበያ መሰረተ ልማት ስብራት ለመጠገን በተሰራው ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።

ከ1 ሺህ 500 በላይ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላትን በማደራጀት አምራችና ሸማቹ የሚገናኝበት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን አብራርተዋል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት የንግዱ ማህበረሰብ በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ለማሳለጥ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው፤ ለዚህም የማዕድን፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የኤሌክትሪክ ግብይት የምርት ውጤቶች ቁልፍ ሚና አበርክተዋል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አቅምን በማሳደግ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል መሰረት መጣሉን አስታውሰው፤ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት እልባት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ስኬታማ ድርድሮች ተደርገዋል ብለዋል።

በመጪው መስከረም በጄኔቫ በሚካሄደው 6ኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያን የድርጅቱ አባል ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመላክ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

Exit mobile version