አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የተገኘው ውጤት በቀጣይ ለሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በራስ መተማመንን የሚፈጥር ነው አሉ ምሁራን።
ምሁራኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ግድቡ የሚገኝበት ምዕራፍ ኢትዮጵያ የመፈጸም አቅሟ የደረሰበትን ደረጃ ያሳያል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጣባባቂ ፕሬዚዳንትና የውሃ ዲፕሎማሲ ምሁር አብደላ ከማል (ዶ/ር)፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተባብረው የግድቡን ፕሮጀክት የብሔራዊ ኩራት እና የራስ መተማመን ምልክት አድርገውታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የተሰነዘሩበትን ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተቋቁሞ ለስኬት መብቃቱን ገልጸው፤ ይህም ለቀጣይ ፕሮጀክቶች ፈተናን መሻገር እንደሚቻል ማሳየቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቶቿን አልምታ ለመጠቀም ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረዉም ተናግረዋል።
ሁለተኛው ዓድዋችን የሆነው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት እና መቻል ለዓለም የገለጠ ነው ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ መምህሩ ጥላሁን ሊበን ናቸው።
እያንዳንዱ የህዝብ ተሳትፎ ግንባታውን ከመደገፍ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን የጸና ፍቅር እና ቁርጠኝነት ያሳዩበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ግድቡ ህልማችን እና ማንነታችን የተንፀባረቀበት የትብብር ታሪክ ነው ያሉት ምሁራኑ፤ በሀገር ፍቅር፣ ትብብርና በጋራ ተሳትፎ የተገኘው የፕሮጀክቱ ስኬት ለመጪው ትውልድ የተበረከተ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።
በመቅደስ የኔሁን
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!