Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ …

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ መውሰድ የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አትሌት ነው – ኢትዮጵያዊው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ፡፡

በድል ላይ ድል በመቀዳጀት እናት ሀገሩን ከተመኘው በላይ ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጎ ያለፈ የአትሌቲክሱ የዘመናት ጀግና ነው፡፡

ከሀገሩ ልጆች ባሻገር አፍሪካውያን በኦሎምፒክ መድረክ ከፍ ብለው እንዲታዩና በድል እንዲደምቁ ፈር ቀዳጅ የአሸናፊነት አብነት ነው፡፡

በፈረንጆቹ 1960 በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ የኦሎምፒክን ክብረወሰን በመስበር ጭምር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝብ ድል ማብሰር ችሏል፡፡

ከውድድሩ አስቀድሞ ፈጽሞ ለአሸናፊነት ያልተጠበቀው አትሌት አበበ በቂላ ድል ማድረጉ በወቅቱ መነጋገሪያ አድርጎት ነበር፡፡

የጣልያን ጋዜጦች በድሉ ማግስት “ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር በርካታ ወታደር አስፈልጓት ነበር ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረች” በማለት ስለ አስደናቂው ድል ማስነበባቸው ይነገራል፡፡

የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የሮም ገድል ብዙ አፍሪካውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ ዕድል የፈጠረና ለድል ያነሳሳ ነበር፡፡

አበበ ቢቂላ በሮም በተቀዳጀው ድል የተደመመው የስፖርት ቤተሰብ በፈረንጆቹ 1964 በቶኪዮ ኦሎምፒክ ዳግም እሱን ለመመልከት በጉጉት ሊጠብቀው ግድ ብሎታል፡፡

ነገር ግን የቶኪዮ ኦሎምፒክ በተቃረበበት ጊዜ አበበ ቢቂላ ልምምድ ላይ እያለ ያጋጠመው ሕመም አብዝቶ ሲጠብቀው የነበረውን የስፖርት ቤተሰብ ያሳዘነ ነበር፡፡

አበበ ቢቂላ ከኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ጋር ወደ ቶኪዮ ቢጓዝም ውድድሩ ላይ ይሳተፋል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም፡፡

ጀግናው አትሌት ግን ከ41 ሀገራት ከተውጣጡ 79 ተወዳዳሪዎች ጋር ተወዳድሮ በድጋሚ ድል ከመቀዳጀት ባለፈ የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ሌላ ታሪክ መጻፍ ችሏል፡፡

አበበ በቶኪዮ ያሳየው ብቃት የኦሎምፒክ ማራቶን አስደናቂ ውድድሮች ተብለው በመጽሃፍ ከታተሙት ታሪኮች ውስጥ ዋና ተጠቃሽ መሆን የቻለ ሲሆን፥ እንከን የለሽ የማራቶን ሯጭ የሚል ስያሜ አስግኝቶለታል፡፡

2ኛውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በአዲስ አበባ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የጀግና አቀባበል የተደረገለት ጀግናው አትሌት፥ ከአቀባበሉ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሻምበልነት ማዕረግና አዲስ ቮልስ ዋገን መኪና ሸልመውታል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ ከእነዚያ ደማቅ ድሎች በኋላ በአንድ ወቅት መኪና ሲያሽከረክር ባጋጠመው አደጋ ከወገቡ በታች ጉዳት ደርሶበት እግሮቹን ማንቀሳቀስ የማይችለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡

ከአደጋው በኋላ እነኚያ ዓለምን ያስደነቁ እግሮች ዳግም መራመድ ባይችሉም የአትሌትነትና የስፖርተኛነት መንፈሱ እንደ ወትሮው ብርቱ ነበር፡፡

በተሸከርካሪ ወንበር አካል ጉዳተኞች በሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ በሌላ መድረክ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ አድርጓል፡፡

አበበ ቢቂላ ከኦሎምፒክ ድሎቹ በተጨማሪ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ ድል ማድረግ የቻለ አትሌት እንደነበር ይታወሳል፡፡

በጃፓን ቶኪዮ ሰርቶ ያለፈውን ታሪክ ለመዘከር በማለም በጃፓን ካሳማ ከተማ ባሳለፍነው ሰኞ የመታሰቢያ መንገድ በስሙ ተሰይሞለታል፡፡

ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በሰራቸው ገድሎች ከዘመን ዘመን ሲወደስ የሚኖር ህያው ጀግና አትሌት ነው፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

Exit mobile version