Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባን ለመኖር ምቹና አካታች ልማት ያላት ከተማ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባን ለመኖር ምቹና አካታች ልማት ያላት ከተማ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝ ጌት የተከናወነውን የኮሪደር ልማት በዛሬው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን ምረቃ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የመዲናዋን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለ እረፍት በትጋትና በጽናት እየተሰራ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት የተመረቀው ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝ ጌት ኮሪደር በሁለተኛው ዙር ከተጀመሩ ስምንት ኮሪደሮች አምስተኛው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የተሰሩ የባቡር መስመር እና ሕንጻዎቹ ወደ መንገድ ተጠግተው መሰራታቸው የኮሪደር ልማት ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኮሪደር ልማቱን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቁመው ÷ ቦታው የእግር ኳስ ሜዳ፣ የመዝናኛ ካፍቴሪያ፣ የልጆች መጫወቻ ቦታ እና ሌሎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
ከ51 እስከ 60 ሜትር ስፋት ያለው 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የዋና መንገድ፣ 16 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት የእግረኛ መንገድ፣ የድጋፍ ግምብ እና የመንገድ ዳር ስማርት ፖሎች እንደተገነቡለትም ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር፣ የባቡር ሀዲድ ላይ የተሽከርካሪና የእግረኛ ማቋረጫ፣ አመቺ የእግረኛና የሳይክል መጋለቢያ መንገዶችን ይዟል ነው ያሉት፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራው በአንደኛ ዙር በተለያየ አቅጣጫ የተጠናቀቁ የኮሪደር ልማቶች ጋር ትስስር የተፈጠረበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመዲናዋ በሁሉም ቦታዎች የተሰሩ ልማቶች አዋቂዎችን፣ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ለነዋሪዎች በሁሉም ዘርፍ ምቹ የሆነች ከተማን ለመገንባት ቅድሚያ እንሰጣለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በህብረት ከተሰራ የኢትዮጵያ ከፍታ በፍጥነት እውን ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ÷ ለዚህም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version