Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ውጤታማ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት…

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ የስፖርት ዘርፉን ውጤታማነት ለማስጠበቅ ተተኪ ስፖርተኞች ላይ መስራት ይገባል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ መክዩ መሐመድ፡፡

ሚኒስቴሩ “የተተኪ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ከአጋር አካላት ጋር መክሯል፡፡

አቶ መክዩ መሐመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ስፖርት ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ ሀገራዊ አሸናፊነትና ክብር ለመጎናጸፍ እንዲሁም ሕዝባዊ አንድነትን ለማጠናከር ሚናው ጉልህ ነው፡፡

ይህንን ውጤት ለማግኘትም ዛሬ ላይ የታዳጊ እና ተተኪ ስፖርተኞች ላይ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ተተኪ ስፖርተኞች ላይ ሳይሠሩ ውጤት መጠበቅ ባዶ ሕልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ የስፖርት ዘርፉን ውጤታማነት ለማስጠበቅ ተተኪ ስፖርተኞች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት የታዳጊ ስፖርተኞችን ልማት በሚያሠራ የሥርዓት መመሪያ፣ ስታንዳርድ እና ማንዋል በመምራት ለአሸናፊነት የሚያበቃ ሥራ ለማከናወን ቁርጠኞች ነን ብለዋል፡፡

ስፖርት ሕዝባዊ መሠረት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቁመው ÷ ሕዝባዊ መሠረት የስፖርት ልማት የጀርባ አጥንት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

ስፖርት በተጠና እቅድ ከታች ጀምሮ የሚተገበር እንጂ በግምትና በደስ አለኝ የሚሠራ እንዳልሆነ አጽንኦት መስጠታቸውንም ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

Exit mobile version