Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማንሰራራታችን ሂደት ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን የሚተርፍ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማንሰራራታችን ሂደት ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን የሚተርፍና ለዓለም የሚነገር ምስክርነት ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ለመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከ25 ሺህ በላይ እንግዶች የሚሳተፉበት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያ በጉባዔው መሪ ሃሳብ መሠረት ለአየር ንብረት መዛባት መፍትሔ ይሆናሉ ያለቻቸውን ተግባራት ጥንቅቅ አድርጋ እየሰራች መሆኗን በኤግዚቢሽን ተሳትፏችን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አስረድተናል ብለዋል፡፡

እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግ፣ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ስራ ለመስራት አዲስ አበባ ማሳያ የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ይዛ መቅረቧን ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካውያን የብልጽግና በር እና የምቾት ቤት መሆኗን ያወሱት ከንቲባዋ፥ በጋራ መምከራችን ለመጪው የአፍሪካውያን መፃኢ ዕድል መሠረት ይሆናል ነው ያሉት።

የከተማዋ ነዋሪዎች በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነና የትብብር መንፈስ እስካሁን ሲያደርጉት የቆዩትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version