Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባዔ ኢትዮጵያ ያሳካቻቸው ልምዶችን የምታካፍልበት መድረክ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምታስተናግደዉ 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባዔ ሀገራችን ያሳካቻቸው ተጨባጭ ልምዶችን የምታካፍልበት መድረክ ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ከዛሬ ጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 2ኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየሠራች ትገኛለች ብሏል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ኢትዮጵያ የምታስተናግደዉ 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባዔ ሀገራችን ያሳካቻቸው ተጨባጭ ልምዶችን የምታካፍልበት መድረክ ነው፡፡

2ኛዉ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ የምታስተናግደዉ ለተሳታፊዎች ተጨባጭ ልምዶችን በማካፈል ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየሠራች ትገኛለች፡፡ መላዉ ኢትዮጵያውያን በተከታታይ ዓመት በሚያደርጉት የላቀ ተሳትፎ የራሳቸዉን ክብረ ወሰን እያሻሻሉ በአንድ ጀምበር ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችለዋል፡፡ ይህም ለዓለም ትምህርት መኾን የሚችል ተነሣሽነትና ቁርጠኝነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ነባር ከተሞችን በማዘመን የውኃ ብክለትን ለመቆጣጠር በሰፊዉ እየሠራች ነው፡፡ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማትን ብቻ ብንወስድ ከእንጦጦ ከፍተኛ ቦታዎች የሚነሡ የአዋሽ ተፋሰስ ገባር ወንዞችን በተሳካ ኹኔታ እያከመች ነው፤ ይህም አጠቃላይ የአዋሽ ወንዝን የማከም አካል ተደርጎ የሚወሰድ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ ወንዞቻችን ንጹሕ፣ ማራኪና ለመናፈሻነት የሚመረጡ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራታችን ለሌሎች አገራት በትልቁ አስተማሪ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በልዩ ትኩረት በማምረትና በመጠቀምም አብነት መኾን የምትችል ሀገር ናት፡፡ ከተሞቿ እና ኢንዱስትሪዎቿ በስፋት የሚጠቀሙት ኃይል ከውኃ፣ ከነፋስ እና ከፀሐይ ኃይል የሚመነጭ ነው፡፡ ከራሷ አልፋ ሌሎች የቀጣናዉን ሀገራት የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግም ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ጉልህ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ የምታመነጫውን ታድሽ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በማጋራት መሰረተ ልማትና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በቀጣናው ሀገራት መካከል ትስስርና ቅንጅት እየፈጠረች ነው፡፡ እንደ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ እና ታንዛንያ ያሉ አገራት ከኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ከኾኑ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በስፋት በመጠቀሟ ለማገዶ ሲባል የሚጨፈጨፍ ደንን በእጅጉ ቀንሳለች፡፡ የበካይ ጋዝ ምንጭ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን መጠን ለመቀነስ እና በሂደትም በታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ለመተካት በስፋት እየሠራች ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከ100 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

መንግሥት በልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ኹሉም የተሽከርካሪ ባለቤቶች ወደ ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት እንዲገቡ እየሠራ ነው፤ ይህም በጉባኤዉ ተሳታፊዎች ልምድ እንደሚወሰድበት ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን ስታስተናግድ ጉባኤዉ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦዋ ኢንምት ኾኖ በጉዳቱ ክፉኛ እየተጎዳች መኾኑ ታውቆ የማካካሻ እና የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንዱኾን አበክራ ትሠራለች፡፡

ኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ቢኖረንም አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ደግሞ እንደ ቤተሰብ በማስተናገድ ቆይታቸው ያማረ እና ፍሬያማ እንዲኾን እናደርጋለን፡፡

ጳጉምን 3/2017 ዓ/ም
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version